“12 Rules For Life“ ከሚለው በ Jordan Peterson የተጻፈው መጽሐፍ የተወሰዱ 12 አንኳር ትምህርቶች

You are currently viewing “12 Rules For Life“ ከሚለው በ Jordan Peterson የተጻፈው መጽሐፍ የተወሰዱ 12 አንኳር ትምህርቶች
Jordan Peterson, 12 Rules for Life

ትርጒም በብሩክ በየነ

1) ወገብህን ታጠቅህ አንገትህን ቀና አድርገህ ሕይወትን ተጋፈጣት

ድሃና ጭንቀትም ሰው ከሰው ቀድሞ በገፍ ይሞታል። ከበሽታ አምጪ ተሕዋሲያን ጋር ግንኙነት በሌላቸው የበሽታ ዓይነቶች ከሌሎች ይልቅ የመያዝ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ፈረንጆቹ “መኳንንቱ ጉንፋን ሲይዛቸው አሽከሮች በሳንባ ምች ያልቃሉ” የሚል ተረት አላቸው። ባጭሩ በኛው አገር አባባል “የተከፋ ተደፋ” የሚለው ማሰቡ ዋናውን ርዕስ ይገልጸዋል። ስለዚህ ወዳጄ ብዙም አትከፋ፣ ቀድመህ እንዳትደፋ የመጽሐፉ ቁጥር አንድ ምክር ነው።

2) ራስህን በራስህ ልክ አደራ እንደተሰጠው ሰው አድርገህ ተንከባከበው

ሰዎች ለራሳቸው ጤና ከመጨነቅ ይልቅ የሌሎችን ጤና መንከባከብ ላይ ሲበረቱ ይታያሉ። ሁልጊዜ የወደፊቱ ሕይወትን አስብና ራስህን “ራሴን በሚገባ ካልተንከባከብኩ ምን ችግር ሊያጋጥመኝ ይችላል?” በማለት ጠይቀው።

3) ላንተ ጥሩ የሚመኙልህን ሰዎች ብቻ ጓደኛ አድርጋቸው

ጓደኝነት ባለሁለት አቅጣጫ መንገድ ነው። ዓለምህን እያጨለመብህ ያለን ሰው የመደገፍ የሞራል ግዴታ የለብህም። እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ ላንተ በጐ፣ በጐውን የሚመኙትን ሰዎች ብቻ ለጓደኝነት መምረጥና በዙሪያህ ማሰባሰብ ይኖርብሃል።

4) ራስህን አሁን ከምታየው ሌላ ሰው ጋር ሳይሆን ትላንት ከነበረው የገዛ ራስህ ማንነትህ ጋር ብቻ አነጻጽረው

እንደ ሁሉም ሰው አንተም የራስህ ችግሮች ይኖሩሃል። የገዛ ራስህን ጉዳይ አንተው ራስህ ተወጣው፣ ከጎንህ ያለው ሰው እየሄደበት ያለውን መንገድ ቀናነት ከማየት ተቆጠብ። ያ መንገድ ለርሱ ብቻ የተፈቀደ ነው።

5) ልጆችህ እንድትጠላቸው የሚያደርግህን ምንም ነገር እንዲያደርጉ አትፍቀድላቸው

ብዙ ወላጆች ከምንም ነገር በላይ የልጆቻቸውን ልብና ቀረቤታ ማግኘት ይፈልጋሉ፤ ለዚህም ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ናቸው። ይሄ ጥሩ አካሄድ አይደለም።

6) የጎረቤትህን ቤት ከመተቸትህ በፊት የገዛ ቤትህን ገበና አስወግድ

ያለህበትን ሁኔታ በደንብ አጢነው፣ በትንሹ ለውጦችን ማድረግ ጀምር፣ በዙሪያህ ያሉትን ዕድሎች በሙሉ አሟጠህ ተጠቅመህባቸዋል? ትክክል እንዳልሆነ አንተ ራስህ የምታውቀውን ነገር ዳግመኛ መልሰህ ከማድረግ ራስህን ዐቅብ።

7) ለጥቅም ብለህ ሳይሆን ለሕይወትህ ትርጒም ያለውን ነገር ብቻ አድርግ

የልብህን ጥሪ አዳምጥ፣ አሁንን ብቻ ለመኖር ሞክር። ለሕይወታችን ትርጒም ያለውን ነገር ለማግኘት ስንል ጊዜያዊ ደስታ ከሚሰጠን ነገር መቆጠብ አለብን። ይህም ማለት ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት ተብሎ ዘለቄታ ያለው መንፈሳዊ እርካታ የሚያስገኝልን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ ማለት የለብንም።

8) እውነቱን ብቻ ተናገር ወይም ቢያንስ አትዋሽ

እነዚህ ሁለት የተለያዩ ምርጫዎች አይደሉም። ሁለቱም የተለያዩ ሁለት የሕይወት ጎዳናዎች ናቸው።

ሌሎች ያንተንን ማንነት እንዲያውቁ ካላደረግክ በቀር አንተም ራስህ ራስህን ማወቅ አትችልም።

9) እያዳመጥከው ያለኸው ሰው አንተ የማታወቀው አንዳች ነገር እንደሚያውቅ ሁልግዜ አስብ።

ሁሉም ሰው አንተን የሆነ ነገር ሊያስተምርህ እንደሚችል የምታምን ከሆነ፣ ራስህን ለማሻሻል፣ ለዕድገት ዝግጁ አድርገሃል ማለት ነው። በዚህም ከእያንዳንዱ ሰው ጋር በተገናኘህ ቁጥር አንዳች አዲስ ነገር በመማር የተሻልክ አንተ መሆንህን በየቀኑ ታስቀጥላለህ ማለት ነው።

10)ስትናገር እንቅጩን ብቻ ተናገር

ችግሩን በግልጽ መናገር፣ ችግሩ እንዳለ ማመን ነው፣ ይህ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

11) እየተጫወቱ ያሉ ሕፃናትን ጨዋታቸውን አታቋርጣቸው

አእምሮህ ሳይበስል በዕድሜ ስትገፋና ስታረጅ፣ እርባና ቢስና ጠባይህ ለሰው የማይመች ሰው ትሆናለህ። ምንም ዓይነት ነገር ያንተ ጥፋት እንደሆነ አድርገህ ለመቀበል ይከብድሃል። ቁጭ ብለህ ብቻ ለእያንዳንዱ ጥፋት ጥፋቱን የምታላክክበትን ስው ስትፈልግ ትኖራለህ።

12) ሁልጊዜም ቀናውን ነገር ከማድረግ አትቆጠብ

በምድር ላይ የመፈጠራችንና ሁሌም በችግር ውስጥ የመኖራችን ምሥጢር ምናልባት ሰው የመሆናችን ምሥጢር ሊሆን ይችላል። ይህን አምኖ መቀበል ቁጭ ብሎ ለምን እንደዚህ ይሆናል ብሎ ከመቆዘም ይልቅ ሳያዋጣ አይቀርም።

ምን ዓይነት ስሕተት እየሠራህ እንደሆነ ካላወቅክ በቀር ራስህን ማሻሻል አትችልም።

Leave a Reply