በትርጒም ፕሮጄክቶች ላይ ተባብሮ የመሥራት አስፈላጊነት

You are currently viewing በትርጒም ፕሮጄክቶች ላይ ተባብሮ የመሥራት አስፈላጊነት
ትርጒም ፕሮጄክቶች The Power of Collaboration

መግቢያ

ወደ አንድ መንደርነት እየተቀየረች ባለችው በርካታ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ዓለማችን የትርጒም ሥራ አንዱና ዋንኛው የተግባቦት መሣሪያ ነው። ከአንዱ ቋንቋ ወደ ሌላው የጽሑፍ መልእክት በሚተላለፍበት ወቅት የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት እንዲቻል ከፍተኛ ፍጹምነትን ይጠይቃል። የትርጒም ሥራ አንድ ሰው ብቻውን ሊሠራው የሚችለው ሥራ አይደለም። ከፍተኛ ጥራት ያለው ትርጒም ሥራ እንዲሠራ ከተፈለገ በቡድን ተባብሮና የተለያዩ ኃላፊነቶችን ወስዶ በአንድነት መሥራት ግድ ይላል። በዚህ ጦማራችን፣ ተባብሮ መሥራት በትርጒም ሥራ ፕሮጄክቶች ላይ ያለውን ፋይዳ እንዲሁም ትርጒም ሥራ ሲሠራ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እና አብሮ ተባብሮ የመሥራቱን ጠቀሜታ ለማሳየት እንሞክራለን።.

ለእያንዳንዱ ፕሮጄክት ፕሮፌሽናሎችን የያዘ ቡድን የማዋቀር አስፈላጊነት

ውጤታማ የትርጒም ሥራ እንዲሠራ ከተፈለገ ሙሉ ጊዜያቸውን እና ትኩረታቸውን የሚሰጡ ፕሮፌሽናሎችን የያዘ ቡድን ማዋቀር የመጀመሪያው የሥራው ምዕራፍ ይሆናል። ቡድኑ ተርጓሚዎችን፣ ገምጋሚዎችን፣ አርታዒያንን፣ ፕሮጄክት አስተዳዳሪዎችን፣ የፕሮጄክት አካውንት ኃላፊዎችን፣ እና የፊደልና ሥርዓተ ፊደል ለቀማ ሠራተኞችን ያካትታል። ዓለም አቀፉ የጥራት ቁጥጥርና ማረጋገጫ ሰጪ ድርጅት (ISO) ጥራትን ለመቆጣጠርና መልእክቶች ከአንዱ ወደ ሌላው በተሳካ መንገድ መተላለፍ እንዲችሉ አንድ የትርጒም ሥራ በሚከናወንበት ወቅት እነዚህን ባለሙያዎች ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ አበክሮ ይመክራል። እያንዳንዱ ባለሙያ በትርጒም ሥራው ፕሮጄክት ውስጥ የሚኖረው ሚና እኩል ፋይዳ አለው።

የትርጒም ቡድኑ ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊነታቸው

ተርጓሚዎች ዋናው ሰነድ በጥንቃቄ በማንበብ፣ ወሳኝ የሆኑ እና ቴክኒክ ቃላትን በመምረጥ በተቀባይ ቋንቋው አቻ የቃላት ፍቺዎችን የያዘ ሙዳየ ቃላት በማዘጋጀት ትርጒም ሥራውን ሠርተው ያስረክባሉ። በማናቸውም ጊዜ ግብረመልስ ሲሰጣቸው የትርጒም ሥራቸውን ያሻሽላሉ፣ ያስተካክላሉ።

ገምጋሚዎች የትርጒሙን ትክክለኛነትና ወጥነት ያረጋግጣሉ። የተተረጎመው ሰነድ በተቀባዩ ቋንቋ ለዛ፣ ሰዋስውና ሥርዓተ ነጥብ ተጠቅሞ የዋናውን ሰነድ በትክክል ማስተላለፍ መቻሉን ያረጋግጣሉ።

አርታዒያን በበኩላቸው ዋናውን ሰነድ (ምንጩ ቋንቋ) ማየት ሳይገደዱ በትርጒም የተዘጋጀው ሰነድ ወጥ ፍሰት እና ግልጽነት የተላበሰ ስለ መሆኑ ከተቀባዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችና በደንበኛው ዒላማ ከተደረጉት ታዳሚያን (ተደራሲያን) አንጻር ትርጒም የሚሰጥና ተነባቢ መሆን አለመሆኑን ያረጋግጣሉ። የመልእክቱ ይዘት ላይ በማተኮር ትርጒሙ በደንበኛው ፍላጎትና ትዕዛዝ መሠረት መሠራቱን በማየት ይሁንታቸውን ይሰጣሉ።

ፕሮጄክት አስተዳዳሪዎች የትርጒሙን ሥራ ፕሮጄክት ከጅማሬ እስከ ፍጻሜው በበላይነት ይቆጣጠሩታል፤ ቀነ ገደቦች እና የተቀመጡ የጥራት መስፈርቶች መከበራቸውን ያረጋግጣሉ።

የፕሮጄት አካውንት ኃላፊዎች ከደንበኞች ጋር በቅርበት በመነጋገር ደንበኞች ከትርጒም ሥራው ምን እንደሚጠብቁ ፍላጎታቸውን እንዲገልጹ በማድረግ ፕሮጄክቱ በተፈለገው በጀትና የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ መቻሉን በበላይነት ይመራሉ። ከደንበኞች ጋር በመሆን ተፈጻሚ ሊሆን የሚችል ዕቅድ፣ የጊዜ ሰሌዳና በጀት ያረቃሉ እንዲሁም ለደንበኞች ፕሮጄክቱ ያለበትን ደረጃ ወቅታዊ ሪፖርት ይሰጣሉ።

የፊደልና ሥርዓተ ፊደል ለቀማ ሠራተኞች የመጨረሻውን ሰነድ ከፊደልና ሥርዓተ ነጥብ ስሕተት ነጻ መሆኑን ያረጋግጣሉ፣ የትርጒሙ ሰነድና ዋናው ሰነድ በመልክ መመሳሰላቸውንና ሥዕሎች፣ ሰንጠረዦች ወዘተ በአግባቡ ቦታቸውን መያዛቸውን ያረጋግጣሉ።

ተባብሮ የመሥራት አስፈላጊነትና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች

የተሻለ የትርጒም ጥራትና ውጤታማነትን ከማስገኘቱ፣ የተሻለ የመልእክት ልውውጥና ተግባቦት እንዲሁም የተሻለ መፍትሔ አሰጣጥ እንዲኖር ከማድረጉ ባሻገር ተባብሮ መሥራት በትርጒም ፕሮጄክት ሥራ ላይ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል። ተባብሮ በመሥራት ትርጒሙ በሰው አቅም ሊኖረው የሚችለውን ከፍተኛ የጥራት ደረጃ እንዲኖረው በማድረግ ደንበኛው በሥራው እንዲረካ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ይሁንና ትርጒም ሥራውን ተባብሮ ለመሥራት በሚሞከርበት ወቅት በብዛት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም። ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል በቋንቋ አለመግባባት፣ የባህል ልዩነት እና እርስ በራሳቸው የሚጣረሱ የሥራ መርሐ ግብሮች በተመሳሳይ ጊዜ መጋጠም ይገኙባቸዋል።

እነዚህ ተግዳሮቶች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ተግዳሮቶቹን በብቃት ለመቋቋምና በውጤታማነት ለማለፍ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን መንደፍና አስቀድሞ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ግድ ይላል። ከነዚህ ስትራቴጂዎች መካከል አንዱ ሥራው በሚከናወንበት ወቅት በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል ውጤታማ የሆነ የመልእክት ልውውጥና ተግባቦት መኖሩን ማረጋገጥ መቻል ነው። ማን ከማን ጋር መልእክት እንደሚለዋወጥ በግልጽ በማስቀመጥ ባለድርሻ አካላት ወቅታዊና አስፈላጊ ግብረመልስ ሳይውል ሳያድር በአግባቡ እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል። ከዚሁ ጎን ለጎን ግልጽ የሆኑ ግቦችን ማስቀመጥና ተፈጻሚ ሊሆን የሚችል የጊዜ ሰሌዳን መቅረጽ የዚሁ ውጤታማ የሆነ የመልእክት ልውውጥና ተግባቦትን የማረጋገጥ ስትራቴጂ ክፍሎች ናቸው።

ቀና የሆነ የሥራ ድባብን መፍጠር በትብብር ሥራ በሚሠራበት ወቅት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የሚያስችል ሌላው ስትራቴጂ ነው። የሚፈለገውን የባለሞያዎች ቡድን ማዋቀር፣ እና አስፈላጊውን ሥልጠና መስጠት የቡድኑን ውጤታማነት የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ ልዩ ክኅሎቶችን እና ውጤታማ አመራር እንዲኖር ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪ እጅግ የላቀ ተግባቦት፣ ትብብርና ተጠያቂነት በቡድኑ ውስጥ እንዲሰፍን ያደርጋል።

ማጠቃለያ

ስኬታማ ትርጒም ሥራ እንዲሠራ ከተፈለገ ውጤታማ የቡድን ሥራ መኖር ይኖርበታል። ኢትዮስታር የፕሮጄክት አስተዳደር መርሆችንና ጥበቦችን በመጠቀም ለእያንዳንዱ ፕሮጄክት ራሱን የቻለ የባለሙያዎች ቡድን እንዲዋቀር በማድረግ የተሻለ ጥራት ያለው ትርጒም ሥራን ለደንበኞቹ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል።

Leave a Reply