ጉልባን እና ሌሎች ዋንኛ ፭ቱ የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች

You are currently viewing ጉልባን እና ሌሎች ዋንኛ ፭ቱ የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች
የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች

አብዛኛዎቻችን እንደምናውቀው በዐቢይ ጾም ከሰርክ ሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሣዔ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በመባል ይታወቃል። እነዚህ በሰሙነ ሕማማት ውስጥ ያሉት ቀናት የዓመተ ፍዳ እና የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው።ታዲያ በእነዚህ ቀናት የተለያዩ ትውፊታዊና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች ይደረጋሉ። ከነዚህ ክንዋኖዎች ውስጥ ፮ቱን ዋንኛ የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊ ትውፊታዊ ክንዋኔዎች አለመሳሳም፣ አክፍሎት፣ ቄጤማ ማሰር፣ ጥብጠባ፣ ጉልባን እና ሕፅበተ እግር በዛሬው ቀን ጸሎተ ሐሙስ እየተባለ በሚጠራውና ጉልባን በሚበላበት ዕለት ልናታውሳችሁ ወደድን።

፩ ጉልባን

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጀና የጸሎት ሐመስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ መሆኑን ብዙዎቻችሁ አትስቱትም። የጉልባን ትውፊት የሚጀምረው እስራኤላውያን ከግብፅ ወጥተው ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚሄዱበት ጊዜ ጉዞው የተጀመረው ድንገትና በችኮላ ስለነበር ሃይማኖታቸው እንደሚያዘው አቡክተው ጋግረው መብላት የሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ አልነበሩምና ያልቦካ ሊጥ እያጋገሩ ቂጣ ጋግሮ መብላት እና ንፎሮ ቀቅሎ ስንቅ እንዲሆናቸው መያዝ የዐርባ ዓመት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነበር። በመሆኑም ይህን ለማሰብና ለማስታወስ ሲባል በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል። በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን እንዲሁም ቂጣ ጨው በብዛት ይጨመርበታል። እንደሚታወቀው ጨው ውኃ ስለሚያስጠማ በዚህ መንገድ ምዕመናን የእየሱስ ክርስቶስን መጠማት ያስባሉ፣ ያስታውሳሉ። ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ምንጩ የእስራኤላውያን ሆኖ በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ዛሬም ድረስ ሥርዓቱ ይከበራል።

፪ አለመሳሳም

በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መስቀል አይሳለሙም፣ አይጨባበጡም፣ አይሳሳሙም እንዲሁም በትከሻ ሰላምታ አይለዋወጡም። ሰላምታ የማይለዋወጡበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማክሰኞ መክረው ሳይስካላቸው ቀርቶ በመጨረሻ ምክራቸው የሰመረላቸው ረቡዕ ቀን ነው። አሁን ባለንበት ዘመነ ፍዳ ወቅት ሰላምና ፍቅር አለመኖሩን ለመግለጽ ሲባል ምዕመናኑ ሰላምታ አይለዋወጡም። መስቀል አይሳለሙም። ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ ፍቅርና ደስታ ያልታየበት በመሆኑ ይህን ለማስታወስ ሰላምታ መለዋወጥን ምዕመናኑ አይፈጽሙም። በተመሳሳይ መልኩ ይሁዳ እየሱስ ክርስቶስን ለጠላቶቹ አሳልፎ ለመስጠት የተጠቀመበት ዘዴ ጌታውን በመሳም በመሆኑ መሳሳም በዚህ ምክንያት የተከለከለ ነው። በተጨማሪም ኦርቶዶክሳዊያን ዲያቢሎስ ሔዋንን ሰላም ለኪ ብሎ ስላታለላትና በሰው ልጅና በምድር ላይ ፍዳን ማምጣቱን በማስታወስና ይኸው ሰላምታ በይሁዳ በመደገሙ በሰሙነ ሕማማት የሰላምታ ልውውጥ አይደረግም።

፫ ሕፅበተ እግር

ሌላው በጸሎተ ሐሙስ የሚከናወን ሃይማኖታዊ ክንዋኔ ሕፅበተ እግር ነው። እየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና የሐዋርያቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ሕይወት ማሕተም የሆነውን ምሥጢረ ቁርባን ያከናወነው በዚሁ ጸሎተ ሐሙስ ቀን ነው። ሕፅበተ እግር እየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቀን እናንተ ለወንድሞቻችሁ እንዲሁ አድርጎ በማለት የደቀ መዛሙርቱን አግር በማጠቡ ምክንያት የሚከናወን ክንዋኔ ነው። እየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያቶቹን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማረቸው በኋላ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሰጣቸው የኦሪትን መሥዋዕት የሻረው እና መሥዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዚሁ በጸሎተ ሐሙስ እለት ነው።

፬ አክፍሎት

በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምዕመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ብቻ ለቁመተ ሥጋ ከቀማመሱ በኋላ እስከ እሑድ /በዓለ ትንሣዔ/ ምንም ነገር ሳይመገቡ ይቆያሉ። ይህም ክንዋኔ አክፍሎት በመባል ይታወቃል ከዓርብ እስከ ቅዳሜ ሌሊት ለእሑድ አጥቢያ ማክፈል ብዙዎች የሚያደርጉት ሲሆን አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው እስከ እሑድ አጥቢያ ያከፍላሉ። ይህንንም የሚያደርጉት ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ የጌታን ትንሣዔ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሣዔው መቆየታቸውን ለማሰብ የሚከናወን ሃይማኖታዊ ትውፊት ነው።

፭ ጥብጠባ

ሌላው በሰሙነ ሕማማት የሚከናወን ሃይማኖታዊ ክንዋኔ በዕለተ ዓርብ የሚፈጸመው የእየሱስ ክርስቶስ የስቅለቱ መታሰቢያ ነው። ምዕመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ኃጢያት በሙሉ ይናዘዛሉ። ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት እንዲሰግዱ ያዟቸዋል። ጥብጠባው የተግሣፅ ምሳሌ ነው። ጥብጠባው የሚደረግለት ሰው በሕማማቱ ወቅት የፈጸመው በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲልበት ያደርጋል። ጥብጣቤ ማለት ቸብ ማድረግ ማለት ነው። ዕለተ ዓርብ (በስቅለት ቀን) በስተመጨረሻ ከሰርሆተ ሕዝብ (የሕዝብ መሰነባበቻ) ከመደረጉ በፊት በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምዕመን ጀርባው ላይ ቸብ ቸብ መደረጉ በእየሱስ ክርስቶ ላይ የተፈጸመውን ግርፋት ያስተውሳል።

፮ ቄጠማ (ቀጤማ)

በቀዳም ስዑር እየሱስ ክርስቶ በመስቀሉ ለዓለም ሰላምን እንደሰጠ እና ትንሣዔውንም እንደገለጠ በማብሠር ቀሳውቱን ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ አዋዲ/ እያቃጨሉ «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ» የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ። ምዕመኑም ቀጤማውንም በራሳቸው ላይ ያስራሉ። ይህም አይሁድ እየሱስ ክርስቶስን አስቃይተው ከመስቀላቸው በፊት የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስተውስ ነው። 

 ቄጠማው በተጨማሪ የምሥራች ተምሳሌት ተደርጐ ይወሰዳል። ይህም የሚሆነውን በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማያያዝ ነው። በኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት ስለሠሩ በንፍር ውኃ ማለቃቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዟቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለማወቅ ርግብን ከላካት በኋላ ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ስትመለስ በዚህ ቄጠማ ምክንያት የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ኖኅ ተደስቷል።

«ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ ሁሉ በእየሱስ ክርስቶስ ሞት «ሞተ ነፍስ» ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች። ምዕመናንም የምሥራች ምልክት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ላይ ያስራሉ።

ምንጭ፦ በኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት

ግብረሕማማትና ጉልባን

Leave a Reply