በዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ዶ/ር ትምኒት ገብሩን ማሰብ ወደድን

You are currently viewing <strong>በዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ዶ/ር ትምኒት ገብሩን ማሰብ ወደድን</strong>

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በዓለም ዙሪያ ያሉትን ሴቶች ስኬት ዕውቅና እና ተገቢውን ክብር ለመስጠት የምንጠቀምበት የተለየ ቀን ነው። በያዝነው ዓመት ክብረ በዓሉን የኮምፒውተር ሳይንቲስት እና በአርቴፊሻል አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) መስክ ተመራማሪ የሆነችውን ዶ/ር ትምኒት ገብሩን እና ሥራዎቿን ለመዘከር መርጠናታል። 

በአርቴፊሻል አስተውሎት ረገድ ዶ/ር ትምኒት ገብሩ ያበረከተችው አስተዋፅኦ 

ዶ/ር ትምኒት ገብሩ በ Google AI (የጉግል ሰው ሠራሽ አስተውሎት) የምርምር ማዕከል ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ነበረች። በቆይታዋም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥነ ምግባር ላይ ምርምር በሚያደርገው ቡድን ውስጥ የቡድን መሪ ነበረች። ከዚህ በተጨማሪ Black in AI የተባለው ጥቁሮች በሰው ሠራሽ አስተውሎት ምርምር ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለመጨመር የሚሠራ ድርጅት ተባባሪ መሥራች ነች። የዶ/ር ትምኒት ገብሩ ምርምር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ሊኖረው ስለሚገባ ሥነ ምግባር እና አድልዎና መገለል በሚደርስባቸው ማኅበረሰቦች ላይ ሊያደርስ ስለሚችለው ጉዳት ላይ በዋንኛነት ያተኩራል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ከማሳወቅ ረገድ 

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በተለይም ሥር የሰደደውን መድልዎና መገለል ከግምት በማስገባት ሊያደርስ ስለሚችለው ጉዳት በቂ ትኩረት እንዲያገኝ ከማድረግ ረገድ የዶ/ር ትምኒት ሥራ ቁልፍ ሚና አለው። የምርምር ሥራዋ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ሥርዓቶች ዝግጅት ላይ ይበልጥ ግልጽነት እና ተጠያቂነት የመኖሩን አስፈላጊነት አፅዕኖት ሰጥቶ ይሞግታል። ከዚህ በተጨማሪ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ኃላፊነት በተሞላ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል እና ሁሉንም የሰው ልጅ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ለማረጋገጥ ሥነ ምግባራዊ ማሕቀፍ መዘጋጀት እንዳለበት በምርምር ሥራዎቿ አመላክታለች። 

ብዝኃነትና አሳታፊነት እንዲኖር ከመሞገት አንጻር 

ዶ/ር ትምኒት ገብሩ በቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ድምፅዋን ያሰማች የብዝኃነትና የአሳታፊነት የመብት ተከራካሪ ነች። በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ የሚታየውን የብዝኃነት አለመኖር ተቃውማለች። ከዚህ በተጨማሪ ሴቶችና ነጭ ያልሆኑ ሰዎች በአመራር ቦታ ላይ መታየት እንዳለባቸው ሽንጧን ገትራ ስትከራከር ቆይታለች። 

ለዶ/ር ትምኒት ገብሩ የተሰጡ ዕውቅናዎችና ሽልማቶች 

ዶ/ር ትምኒት ገብሩ Computing Machinery’s Grace Hopper Award እና Anita Borg Institute’s Social Impact Award የተባሉትን ሽልማቶች ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን አግኝታለች። ከዚህ በተጨማሪ Fast Company በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴት ሲላት MIT Technology Review ደግሞ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት ሰዋች መካከል አንዷ ናት በማለት ዕውቅና ሰጥተዋታል።

እኛ የኢትዮስታር ትርጒም አገልግሎት ሠራተኞች በያዝነው ዓመት ክብረ በዓሉን የኮምፒውተር ሳይንቲስት እና በአርቴፊሻል አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) መስክ ተመራማሪ የሆነችውን ዶ/ር ትምኒት ገብሩን እና ሥራዎቿን ለመዘከር በመምረጣችን ከፍተኛ ክብር ይሰማናል። ሥራዎቿ በሰው ሠራሽ ቴክኖሎጂ ውስጥ ሴቶችና ጥቁሮች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ፍትሐዊና ርትዓዊ እንዲሆን ከማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ላደረገችውና ለሠራችው ሥራ ሁሉ ልባዊ ምስጋናችንን እያቀርብን በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ምርምር ረገድ የጀመረችውን ከዳር እንድታደርሰው ከልብ የመነጨ ምኞታችንን እንገልጻለን።

Leave a Reply