አገልግሎቶቻችን

I. ግላዊ እና የሰነዶች ትርጉም

የሰነድ ትርጉም ማለት በአንድ ቋንቋ ተጽፎ ያለን ይዘት ወደ ሌላ ቋንቋ መቀየር ነው።ግላዊ ትርጉም ለተለያየ ዓላማ ሊውል የሚችል የግልሰቦች ይፋዊም ሆነ ይፋዊ ያልሆኑ ሰነዶች ትርጉም ነው።

የግል እና የሰነድ ትርጒም ዓይነቶች

  • የኢሚግሬሽን ሰነድ ትርጒም፦ ለቪዛ ወይም ለመኖሪያ / ለሥራ ፈቃድ በውልና ማስረጃ መረጋገጥ ያለባቸው ሰነዶች
  • የትምህርት ማስረጃዎች ትርጒም፦ ሰርተፊኬቶች ኣና ሌሎች በትምህር ተቋማት የተሰጡ የትምህርት ማስረጃዎች
  • የሕክምና እና የክትባት ሰነዶች፦ የሕክምና ምስክር ወረቀትዎ፣ የክትባት ካርድዎ ወደ ሌላ ቋንቋ እንዲተረጐምልዎት ይፈልጉ ይሆናል
  • የልደት፣ የጋብቻ እና የሞት ምስክር ወረቀቶች፦ እነዚህ ሰነዶች ለተለያዩ ጉዳዮች ማስተርጐም ይኖርብዎት ይሆናል። የነዚህ ማስረጃዎች ትርጒም በትክክል እንደሚዘጋጅልዎት ከወዲሁ እናረጋግጥልዎታለን
  • የትምህርትና የሥራ ልምድ ቅጽ (ሲቪ) እና የሥራ ማመልከቻ፦ የወደፊት ሥራ አሠሪዎ ይበልጥ በሚገባው ቋንቋ የእርስዎን የትምህርትና የሥራ ልምድ ቅጽ (ሲቪ) እና የሥራ ማመልከቻ እንዲዘጋጅልዎት እናግዝዎታልን

II. የንግድ እና የድርጅት ትርጉሞች

የድርጅት የትርጉም አገልግሎቶች ከንግድ ሥራ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ትርጉም ይይዛል፦የደብዳቤ ልውውጦች፣ የንግድ ሥራ ስምምነቶች፣ የሂሳብ አያያዝ ሰነዶች ትርጉም።

ለንግድ ተቋማት የሚሠራ ትርጒም ሥራ ብዙውን ጊዜ የደንበኛውን ጥያቄ መመለስ እና ፍላጎቱን ማሟላት የሚችሉ የኛን ምርጥ በተፈለገው ዓውድ የተሻለ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ተርጓሚዎች እንድንጠቀም የሚያስገድድን የትርጒም ሥራ ዓይነት ነው። በዓውዱ ከቴክኒክና ከአካዳሚ ረገድ ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው ተርጓሚዎች እንዲሳተፉ እናደርጋለን። እንዲህ ያሉት ሰነዶች የትርጒም ሥራው ከመጀመሩ በፊት የተለየ ጥንቃቄና በቂ ዝግጅት ማድረግን ይጠይቃሉ። በመስኩ የላቀ ዕውቀት ያላቸው ተርጓሚዎች በቡድን አንድ ላይ በመሰየም ከደንበኛው ጋር በመመካከር በመጀመሪያ ለትርጒም ሥራው አስፈላጊ የሆነው ሙዳየ ቃላት ያዘጋጃሉ። ልክ እንደ ምንጭ ቋንቋው ይዘቱ በዒላማ ቋንቋው ሰነድ ላይ መንጸባረቅ እንዲችል የሥራ ሂደቱ የተለየ ዕውቀትና አሠራር ዘዴ፣ ልዩ ክኅሎትና ተመክሮ አንድ ላይ መዋሃድና እርስ በርስ መናበብ አለባቸው።.

ለንግድ ተቋም ደንበኞቻችን የምንሰጣቸው የትርጒም አገልግሎቶች ዝርዝር እነሆ፦

  • ኦዲዮና ቪዲዮ ትርጒም ሥራ – የቪዲዮ ቃል ትርጒም (ዳቢንግ)፣ የተቀዳ ንግግር ትርጒም፣ የፊልም ጽሑፍ ትርጒም፣ የድምፅ ወምስል ትርጒም (ቮይስ-ኦቨር)፣ እና ድምፅን ወደ ጽሑፍ መቀየር። ደንበኛችን በሚፈልገው ቅርጸት ከራሳችን የቀረጻ ስትዲዮ የሚፈለገውን የመጨረሻ ፋይል ዓይነት አዘጋጅተን ማቅረብ እንችላለን
  • የብሮሹር ትርጒም – የማስታወቂያ ሥራ የሚሠራባቸውን ሁሉንም ዓይነት ትርጒም ሥራዎች ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል ሲሆን ይህም ለምሳሌ ብሮሹሮችን፣ በራሪ ወረቀቶችን፣ የኩባንያ መገለጫ (ካምፓኒ ፕሮፋይል)፣ ፖስተሮችን ወዘተ ያካትታል። እንዲህ ያሉት ትርጒሞች ቴክኒካዊ፣ ሕጋዊ፣ የሕክምና፣ የማርኬቲንግ እና ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ያለው ሥራ ከትርጒም በዘለለ የተርጓሚውን የፈጠራና የሥነ ጽሑፍ ችሎታ የሚጠይቁ ናቸው። የሰነድ ለኅትመት ዝግጅት (ታይፕሴቲንግ) እና የዴስክቶፕ ፓብሊኬሽን ባለሙያዎች እንዲሁም የጽሑፍ እርማት ልሂቃን የተሻለው ሥራ እንዲሠራ በማድረግ ላይ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ
  • የመድን እና የሕግ ነክ ሰነዶች ትርጒሞች – የመድንና የሕግ ሙያዊ የተለዩ ቃላት በእንዲህ ዓይነቱ ሥራ ላይ ፈታኝ ሆነው ይገኛሉ። እዚህ ላይ የምንመድባቸው ተርጓሚዎች የሕግ ዓውዱን፣ ፅንሰ ሐሳቦችን እና ሕጋዊ የአጻጻፍ ሥርዓቶችን በሚገባ የሚያውቁ መሆናቸውን በመጀመሪያ እናጣራለን። ተርጓሚ በቀላሉ ከማይገኝባቸው ቋንቋዎች በስተቀር ቢያንስ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ተርጓሚዎች ሥራውን እንዲሠሩ ይደረጋሉ። የመመሥረቻ ጽሑፍ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ የውስጥ ሕገ ደንቦች፣ የኮርፖሬት ፖሊሲዎች፣ የእሽሙርና የሽርክና ውሎች፣ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች፣ የዋስትና መስጫ ሰነዶች እና የመሳሰሉት በዚህ ምድብ ውስጥ የሚጠቃለሉ ሰነዶች ናቸው።

ባለ ብዙ ቋንቋ ሰነድ ዝግጅት – እንዲህ ያለው ትርጒም ላይ በፊደል ምርጫ፣ የጽሑፍ አቀማመጥ እና ዲዛይን ውበት ላይ እንደ የቋንቋው ሕግና ሥርዓት በደንበኛው ፍላጎት መሠረት መዘጋጀታቸውን እናረጋግጣለን።

ከዚህ በተጨማሪ እንዲህ ያለው ሥራ

  • ያለንን የሶፍትዌር ዕውቀትና ችሎታ በተመረጡት ቋንቋዎች ጠባይና ልዩ ሥርዓት መሠረት የመጠቀም ችሎታችንን የምናስመሰክርበት አጋጣሚ ነው
  • የፈጠራ ባለቤትነት ማስረጃ ትርጒም – እንዲህ ያለው ትርጒም ዓለም አቀፉ ታዳሚ ስለ ፈጠራው የሚገልጸውን ይዘት መረዳት እንዲችል በሚያደርግ መልኩ የፈጠራ ባለቤትነት ፈቃድ ማመልከቻ ዝርዝር ሐተታን የመተርጐም ሥራ ሂደት ነው። ዓለም በአሁኑ ጊዜ ወደ አንድ መንደርነት እየተቀየረች ያለ እንደመሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት እንዲህ ያለው ትርጒም ፋይዳው ብዙ ነው። ተርጓሚዎቻችን በዚህ ዓይነቱ የትርጒም መስክ የተለየ ሥልጠና የወሰዱ ናቸው። በዚህ ዓይነቱ ሰነድ ላይ የሚገኙት ቃላት በከፍተኛ ደረጃ የቴክኒክ ቃላት እንደ መሆናቸው መጠን ተርጓሚው በስፔሻሊስት ደረጃ የሚገለጽ ዕውቀት በዓውዱ ያለው መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ያለውን ተርጓሚ ማግኘት ሳይቻል በሚቀርበት ጊዜ፣ ለሥራው የምንመድባቸውን ተርጓሚዎችና አርታዒያን ለማሠልጠን ከደንበኛችን ጋር በጋራ እንሠራለን
  • የቴክኒክ ትርጒም – እነዚህ ፕሮጄክቶች የተተረጎመውን ሰነድ በግራፊክ ዲዛይነር አማካይነት አስውበን ገጾቹን እንድናዘጋጅ የሚያስገድዱን የሥራ ዓይነቶች ናቸው። በቴክኒክ ትርጒም ሥራ ምድብ ሥር የንግድና ፋይናንስ ትርጒምን፣ የሥልጠና ማቴሪያሎችን እና መመሪያ ጽሑፎችን፣ የሕክምና ሰነዶችን ወዘተ ልናስቀምጣቸው እንችላለን
  • የድር ጣቢያ ትርጒም – እዚህ ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ቃል ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላው ጽሑፍን መተርጐም የሚል አንደምታ ያለው ሊሆን ቢችልም ከደንበኛው ጥያቄ በላይ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀን ጠንቅቀን እናውቃለን። ጥንቃቄ በተሞላ ሁኔታ ከአንዱ ቋንቋና ባህል ወደ ሌላው በሚጥምና ግልጽ በሆነ መንገድ የሚፈለገውን መልእክት ማስተላለፍና ጥሩ ስሜት መፍጠር መቻል እንዳለብን አሳምረን እናውቃለን። ከዌብማስተር ጋር ግንኙነት ያላቸው ቴክኒካዊ ግዴታዎች እዚህ ላይ ከግምት መግባት ያለባቸው ፈታኝ ችግሮች ናቸው

III. ሎካላይዜሽን

ሎካላይዜሽኝ በአብዛኛው ቴክኖሎጂ ነክ የሆኑ ምርቶችን ወይም አገልግሎቶችን የተወሰነ ቋንቋን፣ ባህልን ወይም ዒላማ የሚያደርገውን ማኅበረሰብ “ዕይታ እና ስሜት”  ማዕከላዊ ባደረገ መልኩ ለማመቻቸት የሚደረግ የማስማማት ሥራ ነው።

ሎካላይዜሽን (በተጨማሪ l10n /ኤል10ኤን በመባል ይታወቃል) አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ከአንድ አካባቢ ባህልና ወግ ጋር በሚጣጣም መልኩ አዋህዶ የማቅረብ ሂደት ነው በማለት ሊበየን ይችላል። የሎካላይዜሽን ዓላማ በአንድ ዒላማ በተደረገ ገበያ ውስጥ ምርቱ ወይም አገልግሎቱ በራሱ በገበያው ውስጥ ባሉ ታዳሚዎች ባህልና ወግ ተቃኝቶ በአገሬው ዜጎች እንደተመረተ መስሎ አገልግሎቱ ወይም ምርቱ እንዲቀርብ ማድረግ ነው። በቀጥታ ሎካላይዜሽን ማለት ትርጒም ማለት እንደሆነ ተደርጎ መታሰብ የለበትም። በርግጥ ትርጒም ከሎካላይዜሽን ሥራ እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ አካል ነው። ከትርጒም በተጨማሪ ሎካላይዜሽን የሚከተሉትን ተግባራት ያጠቃልላል፦

  • ዒላማ የተደረጉትን የአካባቢውን ሰዎች ምርጫና ፍላጎት በማክበርና ልዩ ፍላጎታቸውን ከግምት በማስገባት ይዘትን ማጣጣምና ማሻሻል
  • የአካባቢውን ቋንቋ በሚመጥን መልኩ የይዘትን ዲዛይን እና ገጽታ በሚገባ ማንጸባረቅና ማዘጋጀት
  • ቀንና ሰዓት፣ አድራሻ፣ ቁጥር፣ ምንዛሬ ወዘተ አጻጻፍ ሥርዓቶች ከአገሬው ሥርዓት ጋር እንዲጣጣሙ ማድረግ
  • ምስሎችና መሰል ገላጭ አዶዎች የአካባቢውን ባህልና ወግ ያከበሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ
  • እንደ አካባቢው ፊደል ገበታ ቅደም ተከተል መሠረት ዝርዝሮችን በቅደም ተከተል ማዘጋጀት

ሎካላይዜሽን ፕሮጄክት እነዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩ አገልግሎቶችን የሚያካትት አንድ ራሱን የቻለ ጥቅል አገልግሎት ነው፦

  • ሳንካ እርማት (ቅድመ-ምርት፣ በምርት ሂደት ወቅት እና ድኅረ ምርት ክትትል)
  • ኢንተርናሽናላይዜሽን
  • የሎካላይዜሽን ሥራ ተግባራዊ ሙከራ
  • ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ
  • ሶፍትዌር ሎካላይዜሽን
  • ሶፍትዌር ትርጒም ሥራ
  • በተጠቃሚ ዘንድ ተቀባይነት ስለመኖሩ ማረጋገጥ

የሎካላይዜሽን ሥራ ምሳሌ

እንደ ኢትዮስታር ትርጒም አገልግሎት ድርጅት የደንበኞቻችን ምርቶች በይዘት ሎካላይዜሽን ሥራቸው ከሚጠበቀው በላይ ልቀው እንዲወጡና ስኬታማ እንዲሆኑ ለማድረግ አስፈላጊውን በራስ ተነሣሽነት የሚደረግ ክትትል ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አለን። ምርቶች በዓለም አቀፉ ገበያ ነጥረው እንዲወጡና ተወዳጅ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ አስፈላጊውን ጥርጊያ መንገድ በመጥረግ ረገድ ፋና ወጊዎች ለመሆን እንሻለን።

በዓለም ታዋቂ ከሆኑ በሚገባ ጥናት ተደርጎባቸው የሎካላይዜሽን ሥራ ከተሠራባቸው ምርቶች መካከል Coca-Cola (ኮካ ኮላ)፣ Microsoft፣ እና Nike ን እንደ ምሳሌ እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል። በተጨማሪ የሚከተሉት ምርቶች ውጤታማ የሆነ የሎካላይዜሽን ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ተሠራባቸው ምርቶች አድርጎ መጥቀስ ይቻላል።

World Wide Fund for Nature (WWF)፦ ባከናወናቸው ግንዛቤ የማስጨበጫ ዘመቻዎች በተጠቀመባቸው የሎካላይዜሽን ቴክኒኮች አማካይነት እንዴት አንድ ድርጅት መረጃና ዕውቀትን በሚገባ በማስተላለፍ የማኅበረሰብን ማንቃት ሥራ ሊሠራ እንደሚችል ለማሳየት በቁንጮነት የሚቀርብ አብነት ነው።

Airbnb፦ ተገኝነቱን ከ 220 በላይ አገሮች ውስጥ ለማስረፅና ለእያንዳንዱ የጊዜያዊ ቤት ፍላጎት ጥያቄ የግል ፍላጎትን ባመከል መልኩ ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ በማስቻል በዓለም ዙሪያ ያለውን የኣንግዳ አቀባበል ዘይቤ አንዳች ዓይነት የተለየ መልክ እንዲይዝ አድርጓል። የድር ጣቢያቸውንና መተግበሪያቸውን በ62 የተለያዩ ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል።

Netflix፦ለተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ዓይነት ይዘት በማቅረብ በዓውዳቸው በመሪነት ደረጃ ለመቀመጥ ችለዋል፤ ይህ ገጽታቸው በመነሻ ገጻቸው ላይ ከሚሰጡት መታየት ያለበት ፊልም ምክረ ሐሳብ ጀምሮ እስከ የፊልም ትርጒም ጽሑፋቸው ድረስ ይንጸባረቃል።

በዘርፍ የተለዩ ልምድ የሚጠይቁ

IV. የተመቻቹ እና ተጨማሪ ትርጉሞች

የተመቻቹ እና ተጨማሪ ትርጉሞች

  • የይዘት ጽሑፍ አገልግሎት፦ ለድር ጣቢያዎች፣ ለድር ይዘት ጽሑፍ፣ ለማርኬትንግ ይዘት ማቴሪያል፣ ለትርፍ ያልተቋቋም ድርጅት መረጃ መስጫ ሰነድ፣ የጥናትና ምርምር ጽሑፎች፣ የፊደል እርማት ሥራ አገልግሎቶች፣ ኢንፎግራፊክ ይዘት፣ የማኅበራዊ ትስስር አውታር ይዘት፣ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የምርት ዝርዝር መግለጫ፣ የማስታወቂያ ጽሑፍ ዝግጅት፣ እና ተጨማሪ ሌሎች መሰል አገልግሎቶች።
  • ለኅትመት የሚሆን ጽሑፍ አርትዖት፦ የማስታወቂያ ጽሑፍ አዘጋጅ ባለሙያ የሚያዘጋጀው ጽሑፍ በቀላሉ ተነባቢ፣ ትክክለኛ እና ለኅትመት ዝግጁ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት። መጽሐፍ፣ ጋዜጣ እና መጽሔትን ጨምሮ በሁሉም ዓይነት ኅትመት ላይ አገልግሎት ይሰጣሉ። አንድ ጽሑፍ በጥሩ ሁኔታ መጻፉን በአመክንዮዋዊ መንገድ መዘጋጀቱን እንዲሁም ትክክለኛው ሰዋሰውና ሥርዓተ ፊደል ጥቅም ላይ መዋሉን ያረጋግጣል።
  • የማስታወቂያ ጽሑፍ ዝግጅት፦ ለማስታወቂያ ወይም ሌላ ዓይነት የማርኬቲንግ ሥራ ዓይነቶች የሚሆን ጽሑፍን የማዘጋጀት ሥራ ነው። እዚህ ላይ ያለው የትርጒም ሥራ ዓይነት ኮፒ ወይም የሽያጭ ኮፒ በመባል ሲታወቅ የአንድ ምርት በሰዎች ዘንድ ያለ ግንዛቤ ለመጨመርና በመጨረሻም አንባቢው ምርቱን እንዲጠቀም ወይም አንዳች ዓይነት እርምጃ እንዲወስድ ለማሳመን በሚያስችል መልኩ የሚዘጋጅ ነው።
  • የፊደል ዕርማት ሥራ፦ ለምሳሌ ለኅትመት የተዘጋጀ መጽሐፍ ጽፈው ሊሆን ይችላል። የኛ ፊደል ዓራሚዎች መጽሐፉ ለኅትመት በሚዘጋጅበት ወቅት ወይም ሰነዱን ለትርጒም ከመላክዎ በፊት በእርስዎ ወይም በእርስዎ አርታዒ የሆነ ነገር ተሳስቶ እንደሆነ ለማረጋገጥ እንዲችሉ ሊያግዝዎት ይችላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ኅትመት ውጤቶች የመጨረሻ የፊደል ዕርማት ሥራ ባለሙያ ሳያያቸው እንደወጡ ለመታዘብ ችለናል።
  • ዴስክቶፕ ኅትመት ሥራ፦ ጽሑፍንና ምስልን የሚያቀናጅ የዴስክቶፕ ኮምፒውተርን በመጠቀም ለኅትመት የሚሆን ማቴሪያልን የማዘጋጀት ሥራ ነው። ለአጠቃላይ ኅትመትና ግራፊክስ ሥራ (የድርጅት ጋዜጣ፣ መጽሔቶች፣ ብሮሹሮች፣ አነስተኛ መጽሓፍት ወዘተ) እንደ Adobe InDesign፣ Adobe PageMaker እና አልፎ፣ አልፎ ደግሞ ግድ ሲሆን QuarkXPress ን መጠቀም እንችላለን። ረዥም ለሆኑ፣ በርካታ ምዕራፎች ላላቸው ሰነዶች (ለምሳሌ መጽሓፍት፣ አካዳሚያዊ ኅትመቶች፣ እና መመሪያ ጽሑፎች) Corel Ventura፣ Adobe InDesign፣ Adobe FrameMaker እና QuarkXPress ን መጠቀም እንመክራለን። በመጨረሻ ሠንጠረዥ ለሚበዛባቸው ማቴሪያሎች (ሳይንሳዊ ኅትመቶች፣ የቴክኒክና የስታትስቲክስ ኅትመቶች፣ እና ከፍተኛ ውሂብ (ግርድፍ መረጃ) ላለባቸው ኅትመቶች)፣ Corel Ventura፣ Adobe FrameMaker፣ Adobe InDesign፣ እና QuarkXPress የደንበኛችንን ፍላጎት ይበልጥ ሊያሟሉ ይችላሉ ብለን እናምናለን።

V. የማስተርጎም አገልግሎቶች

ማስተርጎም በሁለት የተለያዩ ቋንቋ ተጠቃሚዎች መካከል በቃል ወይም በምልክት ቋንቋ የሚደረግን ተግባቦት ከአንዱ ቋንቋ ወደሌላኛው የማስተርጎም ሂደት ነው።

ትሩጅማን አገልግሎት፦ ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላው ትርጓሜን እና የምንጭ ቋንቋውን ይዘት አንደምታ ጠብቆ ንግግርን ወይም የምልክት መልእክትን የማስተላለፍ ሂደት ነው። ትርጁማኖቻችን በሕግ ተቋማትና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመሳሰሉት በመገኘት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ናቸው።

ሦስት ዓይነት የትርጁማን ሥራ ዓይነቶች አሉ።

  1. ተናጋሪን ዕድል እስኪሰጥ ጠብቆ በንግግር መተርጎም አገልግሎት፦  ትሩጅማኑ ከምንጭ ቋንቋው ተናጋሪ በመለጠቅ ይናገራል። ለዚህ በቴሌፎን የሚሰጥ የትርጒም አገልግሎት እንደ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል። የኛ ተርጓሚዎች ከአንድ አገር ወደ ሌላ መሄድ ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ሆነው በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ ወይም በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያሉ ደንበኞቻችን ከግል ሐኪሞቻቸው፣ ጠበቇቸው ጋር ወዘተ የሚፈልጉትን መልእክት መለዋወጥ እንዲችሉ ያግዛሉ።
  2. እኩል ከተናጋሪው ጋር የሚደረግ የትርጒም አገልግሎት፦ ተርጓሚው ተናጋሪው እየተናገረ እያለ እዛው በዚያው ወዲያውኑ እየሰመ የሰማውን ለአድማጮች ይተረጉምላቸዋል።
  3. ምልክት ቋንቋ፦ በጽሑፍ የቀረበን ይዘት በምልክት ቋንቋ መግለጽ።

ትርጁማኖች በፍጥነትና በቅጽበት ትርጒምና፣ ቅላጼን እና የኦርጂናሉን መልእክት ሐሳብ በዒላማ ቋንቋው በትክክል በሁሉም ዓይነት መላምቶች ውስጥ ሆነው ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል። ትሩጁማን ሥራ እጅግ የላቀ የቋንቋ ችሎትን፣ ለየት ያለ የማስታወስ ችሎታን፣ በፍጥነት ሁኔታዎችን መተንተን መቻልን፣ እና በቋንቋዎች መካከል መልእክትን በትክክል ማስተላለፍን፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርን በጥንቃቄ ማክበርን ይጠይቃል። ከዚህ በላይ እንደተገለጸው፣ ትሩጁማን አገልግሎት ፊት ለፊት፣ እና በርቀት በቴክኖሎጂ አማካይነት ሊከናወን ይችላል። በርቀት የሚደረግ የትሩጁማን ሥራ የቴሌፎንን እና ቪዲዮ መልክእክት ልውውጦችን ማድረግ በሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች (ለምሳሌ Zoom፣ Skype፣ Google Hangouts ወዘተ) አማካይነት ሊከወን ይችላል።

VI. ለደንበኞቻችን የምንሰጣቸው ተጨማሪ አገልግሎቶች፦

ጊዜዎን እና ገንዘብዎን መቆጠብ የሚችሉባአው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የታለሙ ልዩ የአገልግሎት ጥቅሎች አሉን። ቤትዎን ወይም የሥራ ገበታዎን ጥለው መሄድ ሳይኖርብዎት የትርጒም ሥራዎን ማዘዝ ይችላሉ፦

* በበይነመረብ በቀጥታ የትርጒም አገልግሎት አግኝተው በዚያው ክፍያዎን መክፈል ይችላሉ

* ሰነድዎን ተርጒመን በውልና ማስረጃ እንዲረጋገጥ እናስደርጋለን

* ነጻ በስልክ የሚሰጥ የቋንቋ እና የትርጒም አገልግሎት ምክር

 

ፕሮፌሽናል የትርጒም ሥራን በሁሉም ዘንድ ገናና እና የተከበረ ሥራ እንዲሆን እንጥራለን

የእርስዎ ግዴታ አዳዲስ ምርቶችን ወይም አገልግሎቶችን በአገር ውስጥና በባሕር ማዶ ማቅረብ እና በዓለም ደረጃ ንግድ ሥራዎን መሥራት ነው። የእኛ ግዴታ ንግድ ሥራዎ ወደ ተጨማሪ ደንበኞች መተዋወቅ እንዲችል ይዘትዎን በትክክል መተርጐም ነው።

ኢትዮስታር ትርጒም አገልግሎት ድርጅት የእርስዎን ሰነድ፣ ማስታወቂያዎች እና የማስተዋወቂያ ማቴሪያሎች፣ ሶፍትዌር፣ ድር ጣቢያ እና የመሥመር ላይ (ኦንላይን) ይዘት ወደ ዋንኛ የእሲያ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ኣና የአውሮፓ ቋንቋዎች ወይም ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች ወደነዚህ ቋንቋዎች ለመተርጎም የሚያስችሉ ብዝኃነት ያላቸው ልዩ ባለሙያን ያካተቱ የትርጒም አገልግሎቶችን ያቀርብልዎታል። በዚህም አዳዲስ ገበያ እንዲያገኙ፣ የንግድ ሥራዎን እንዲያስፋፉ እና በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተሻለ መንገድ መልእክት መለዋወጥ እንዲችሉ እናግዝዎታለን።

በርካታ የተለያዩ ዓይነት የትርጒም ሥራ አገልግሎቶችን እንሰጣለን

ኢትዮስታር ትርጒም አገልግሎት ድርጅት ከፍተኛ ሥልጠናና ልምድ ያላቸውን በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ተርጓሚዎችን ይጠቀማል። ተርጓሚዎቻችን በፊናቸው ምርጥ ትርጒም ሥራ ማቅረብ መቻላቸውን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ አቋም ያላቸው ናቸው።

ከምናቀርባቸው በርካታ ቋንቋ አገልግሎቶች መካከል የሚፈልጉትን መምረጥ ይችላሉ። የትርጒም ሥራ ቡድናችን የእርስዎ መልእክት በትክክል ለእርስዎ ደንበኞች መተላለፍ መቻሉን ያረጋግጥልዎታል።

የምንሠራባቸው ቋንቋዎች

የኢትዮጵያ ቋንቋዎች፦

የኤርትራ እና ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ቋንቋዎች፦

የኢሲያ ቋንቋዎች፦

የአውሮፓ ቋንቋዎች፦

ያልተለመዱ እና የልዩ ቋንቋዎች አገልግሎት፦