የሎካላይዜሽን ሥራ እንዴት መጀመር ይቻላል? ክፍል 2

በአብዛኛው፣ ሶፍትዌርዎትን ወይም ድር ጣቢያዎን ሎካላይዝ ለማድረግ የሚያወጡት አጠቃላይ ወጪ፣ ሥራው ከሚፈጥራቸው ዕድሎች ከሚገኘው ተመላሽ ያነሰ ነው የሚሆነው። ምርትዎትን ወይም አገልግሎትዎትን ሎካላይዝ ለማድረግ ከወሰኑ፣ ምርቱ ወይም አገልግሎቱ ሎካላይዝ ለመደረግ ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጡ እንዲሁም ሎካላይዜሽኑን ሂደትዎ ውስጥ ያለችግር ለማቀናጀት ትክክለኛዎቹን ማቀናበሪያዎች ይምረጡ።

ስለዚህ፣ መጀመር ያለብዎት ከምንድነው? በክሕሎት በሚሥራ የሎካላይዜሽን ፕሮጀክት ውስጥ በርካታ ክፍሎች በመኖራቸው ይህ አስቸጋሪው ሥራ ሊሆን ይችላል። እንደ አብዛኛዎቹ የንግድ ዘርፎች በትክክል ሊያደርጉት ከፈለጉ፣ ስኬቱ የሚጀምረው ከዕቅድ ደረጃው ነው። የሎካላይዜሽን ስትራቴጂዎን ሲያዘጋጁ ሊጠቀሟቸው የሚገባዎትን ስድስት ጠቃሚ ደረጃዎች ይመልከቱ።

ዕቅድ እና ምርምር

በሚገኙበት ገበያ ውስጥ አንድን ምርት ለመልቀቅ በቅድሚያ ሰፊ ምርምር ማድረግዎት የግድ ነው። በሶፍትዌርዎት ጥራት እና ጥሩ ሽያጭ በማካሄድ ረገድ እርግጠኛ በመሆንዎት ምክንያት ብቻ የውጭ ገበያ ውስጥ ዘው ብለው መግባት አይችሉም። የሶፍትዌር ሎካላይዜሽን ፕሮጀክትዎት በሽያጭ ስኬታማነት፣ ምርት የማስማማት፣ እና መልእክትን በብልሃት የማስተላለፍ ማሳያ ምሳሌ እንዲሆን መፈለግዎት ግልጽ ነው። ከላይ ለተሰጡት ምክንያትኦች እንጂ የዓለም አቀፍ ስኬታማ ያልሆኑ ግብይቶች ዝርዝር ውስጥ የሚያስገባዎት ጉልህ ስብስቦች ስላለዎት ምሳሌ ለመሆን ሊሆን አይገባም። የሶፍትዌር ሎካላይዜሽን ፕሮጀክትዎት ከችግር የጸዳ እና የትክክለኛ ዕቅድ ውጤት መሆኑን ለማረጋገጥ የሚረዱ መከላከያ እርምጃዎች አሉ።

ስለዚህ፣ ስኬታማ የመሆን ጥሩ ዕድል ሊያገኙልዎት የሚችሉትን ገበያዎች ከግምት ውስጥ ያስገቡ። የድርጣቢያዎትን ጎብኚዎች እና የሶፍትዌርዎትን ተጠቃሚዎች ለይተው ይወቁ። ከምሥራቅ አውሮፓ ብዙ ሰዎች ድር ጣቢያዎትን ይጎበኛሉ? ከውጪ ያለዎት የድር ጣቢያ ተመልካች ብዛት በዩናይትድ ኪንግደም የተመሠረተ ነው? ባህሉ ምን ያህል ተመሳሳይነት አለው? ሕጋቸው ምን ዓይነት ነው? ሊያገኟቸው እና ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸው አካባቢያዊ ሀብቶች አሉዎት? በዓለም ዙሪያ ከ 4 ቢሊዮን በላይ የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች አሉ። ነገር ግን ይህ ማለት ሁሉም የእርስዎ ምርት ላይ ፍላጎት ያሳድራሉ ማለት አይደለም። በመጀመሪያ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር በማካሄድ እና ዕቅድ በማዘጋጀት የትኩረት አቅጣጫዎን ለይተው ያጥብቡ።

መልእክትዎትን የሚቀርጹበትን መንገድ በጥንቃቄ ማካሄድ እንዳለብዎት ያስታውሱ። የሶፍትዌር ሎካላይዜሽን ደካማ ሙከራ ማሳያ በሆነው በግማሽ ለግማሽ ብቻ በተተረጎመ ሶፍትዌር ወደ ገበያ መግባት እንደማይፈልጉ ግልጽ ነው። አንድ የተሠራ ጥናት እንደሚያመለክተው የእንግሊዝኛ ቋንቋ መረዳት ከማይችሉ ሰዎች 87 በመቶዎቹ በእንግሊዝኛ ብቻ ከሆነ ድር ጣቢያ ግዢ አይፈጽሙም። ሶፍትዌርዎትን አይጠቀሙም መተግበሪያዎትንም አያወርዱም። በመሆኑም፣ ይዘትዎትን በተመለከተ አቋራጭ ለመጠቀም አለመሞከርዎትን ያረጋግጡ።

በዕቅድ እና ምርምር ደረጃው ላይ፣ እንደ ሶፍትዌር ዲዛይን አቀማመጥ ያሉ ጠቃሚ የሶፍትዌሩን ክፍሎች ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ቋንቋዎች የሚወስዱት የቦታ መጠን የተለያየ ነው። በጥሩ ሁኔታ የሚሠራ ሶፍትዌር አዘጋጅተው ወደ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ወይም ዐረብኛ ሲተረጎም ከአቀማመጥ ዲዛይኑ ጋር የማይጣጣም እንዳይሆን ሊጠነቀቁ ይገባል። በርካታ ውጣ ውረድ ሊያስከትልብዎት ስለሚችል ሊለወጡ የማይችሉ የዲዛይን ክፍሎችን ከመጠቀም ይቆጠቡ።

እንዲሁም፣ በዓለም ዙሪያ ያለውን የበይነ መረብ ፍጥነትም ከግምት ውስጥ ያስገቡ። ሁሉም ሰው አንድ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ጊዜ ማጣቱ እና ትዕግስት አልባነቱ ነው። የንግድ ሥራውን በሚሠሩበት ቦታ ሁሉ ድር ጣቢያዎት በተቻለ መጠን በፍጥነት መክፈት እና መንቀሳቀስ ይኖርበታል። በዚህም ምክንያት ጥሩ ያልሆነ ፍጥነት ያለው አካባቢያዊ የበይነ መረብ መሥመር ለመጠቀም ከተገደዱ፣ ለሁሉም ተጠቃሚ ተፈላጊውን ፍጥነት ለማቅረብ CDN (Content Delivery Network) መጠቀም ይችላሉ። የድር ጣቢያ ፍጥነት የፍለጋ መሣሪያ ደረጃ መስጫ ከሆኑት ነጥቦች መካከል አንዱ ስለሆነ በዚህ ነጥብ ላይ መሥራቱ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

በስተመጨረሻም፣ የሚኖሩብዎትን ወጪዎች ከግምት ውስጥ ያስገቡ። ሶፍትዌርትዎትን ሎካላይዝ ማድረግ በሚፈልጉባቸው ቋንቋዎች ብዛት መሠረት የሎክላይዜሽን ወጪዎት መጨመሩ የማይቀር ነው። ፈሰስ ማድረግ የሚችሉት ከፍተኛ በጀት ከሌለዎት፣ በአንድ ጊዜ ወደ 200 ቋንቋዎች ሎካላይዝ ማድረግ አስፈላጊ አይደለም። ለሎካላይዜሽን ያፈሰሱትን መዋዕለ ንዋይ መመለስ [ROI (Return on Investment)] ይችላል ብለው የሚያስቡትን አንድ ወይም ሁለት ቋንቋ ይምረጡ። ቻይና በዓለም ላይ ከፍተኛ ትርፍ ከሚገኝባቸው ገበያዎች ውስጥ አንዷ ናት፣ ነገር ግን ገበያውን ሰንጥቆ መግባት ከባድ ከሆነባቸውም ተርታ ትሰለፋለች። እንደ Coca Cola፣ McDonald’s እና Google የመሳሰሉ ትልልቅ ድርጅቶች በዚያ ገበያ ውስጥ ችግር ሊያጋጥማቸው ከቻለ፣ እርስዎም ምርትዎን ወደ ገበያው ከማስገባትዎ በፊት ሙሉ ለሙሉ ሊተማመኑበት ይገባል።

የሥራ ቡድኖዎትን መመሥረት

ስኬታማ የሆነ የሎካላይዜሽን ሥራ ጠንካራ የሆነ የሠራተኞች ቡድን ያስፈልገዋል። የሥራ ቡድንዎትን ማዋቀር ከባድ ከሆኑት ተግባራት መካከል ሊመደብ ይችላል። ትክክለኛውን ክሕሎት እና ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች መምረጥዎትን እና እያንዳንዱ የቡድኑ አባል ከሌላኛው ጋር መሥራት መቻሉን ማረጋገጥ ይኖርብዎታል። ሁሉም ሰው ፕሮግራመር አይደለም፣ ሁሉም ፕሮግራመር ደግሞ የቋንቋ ችሎታ አለው ማለት አይቻልም። ይህም ማለት በቡድኑ አባላት መካከል በቀላሉ ቅንጅት ሊፈጠር እንደሚችል ማረጋገጥ ይኖርብዎታል ማለት ነው። አብዛኛው የቡድኑ አባላት በርቀት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ሆነው የሚሠሩ ነው የሚሆነው። አስፈላጊ ከሆነ ፈጠራ የታከለበት ትርጉም ሥራ መሥራት የሚችሉ ተርጓሚዎች ያስፈልጉዎታል። በአካባቢው ማኀበረሰብ ጥቅም ላይ የሚውሉ ኢ-መደበኛ ንግግሮችን እና የቃላትን ትርጓሜ መረዳት እንዲሁም የአካባቢውን ታዳሚያን ቅላጼ እና ድምጸት ማወቅ ይኖርባቸዋል።

ነገር ግን፣ ይህ እንዳለ ሆኖ መሠረታዊ የሆኑ ቴክኒካዊ ክሕሎቶችም ያስፈልጓቸዋል፣ ወይም ቢያንስ መማር መቻል አለባቸው። ስለ ኮምፒውተር ያለው ዕውቀት እምብዛም ለሆነ ሰው ስለ HTML እና ፕሮግራሚንግ ስትሪንጎች (strings) ማውራት ቢጀምሩ ምልልሱ ያን ያህል የሚገፋ አይሆንም። ለዚህም ነው ዩኒኮድ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የሚረዱ እና ዓለም አቀፋዊ ማድረጊያ ቴክኒኮችን መተግበር የሚችሉ ክሕሎቱ ያላቸው የሶፍትዌር አዘጋጆች የሚያስፈልጉዎት።  ነገር ግን፣ የተወሰነ የማኅበራዊ ተግባቦት ክሕሎትም ሊኖራቸው ይገባል። ተርጓሚዎች የሚሠሩበትን መንገድ ሊረዱ ይገባል። የፕሮግራሚንግ ስትሪንጎችን ቀጥታ እንዲተረጎሙ ከማስተላለፍ ይልቅ ስለ ዐውድ አስፈላጊነት ማወቅ ይኖርባቸዋል።

አካባቢያዊ የግብይት አማካሪዎችን እንዲሁም ምናልባት ፀረ-ውድድር ሕጎችን ለማወቅ የሕግ አማካሪዎችም ሊያስፈልጉዎት ይችላሉ። የማስተዋወቅ ገደቦችም ከአገር አገር ይለያያሉ። በመጨረሻም፣ በሥራ አመራር የተካነ ሰው ያስፈልግዎታል። ሁሉም ነገር በትክክል እንዲከናወን ቁልፍ ሚናውን የሚጨወቱት እርስዎ እንደሆኑ መዘንጋት የለብንም።

ትክክለኛውን የትርጉም ሥራ አሠራር ሶፍትዌር (Translation Management Software) መምረጥ

ይህንን እስካሁን ካላወቁ አሁን ማወቅ ይኖርብዎታል። ትክክለኛውን የትርጉም ሥራ አሠራር ሶፍትዌር መጠቀም የሶፍትዌር ሎካላይዜሽን ፐሮጀክትዎትን የሚያሳካው ወይም ውድቅ የሚያደርገው ጉዳይ ነው። ትክክለኛው የትርጉም ሥራ አሠራር ሥርዓት [TMS (Translation Management System)] ቡድንዎን በቀላሉ እንዲመሩ እና ሁሉም በተቀናጀ መንገድ እየሠራ እንደሆነ ለማረጋገጥ የሚያስችሉዎት በርካታ ቁልፍ መገለጫዎች ይኖሩታል። በዓለም ዙሪያ ያለውን ቡድንዎትን በተሻለ ሁኔታ እና በአነስተኛ ወጪ መምራት የሚያስችልዎት በይነ መረብ ላይ የተመሠረተ መተግበሪያ ይፈልጉ።

የራስ-ሠር አሠራርን ሊያቀል የሚችል API (Application Programming Interface) እንዳለው እርግጠኛ ይሁኑ። በሶፍትዌሩ ውስጥ የተዋሃደ API መኖር ፕሮግራመሮቹ አዳዲስ ምርቶችን በቀላሉ ወደ አሠራሩ ውስጥ እንዲያስገቡ ያስችላቸዋል። የሚሠራባቸውን ፋይሎች በቀላሉ እና በፍጥነት ማስገባት መቻል አስፈላጊ ነው። በተለይም ምርትዎትን ወደ በርካታ ቋንቋዎች ሎካላይዝ ማድረግ ወይም ለደንበኞች ተጨማሪ የሶፍትዌር ሎካላይዜሽን ሥራዎችን መሥራት ከፈለጉ ይህ አስፈላጊ ነው። የሚጠቀሙት የትርጉም ሥራ አሠራር ሥርዓት የቡድን አባሎችዎት በቀላሉ መቀናጀት እና መልእክት መለዋወጥ፣ የማያ ገጽ ቅንጥብ ምስል ማስቀመጥ፣ ሰዎችን ልጥፎች ላይ ማስገባት፣ ግብረ መልስ መስጠት እና በአጠቃላይ ፕሮጀክቱን የበለጠ ውጤታማ እንዲሁም ሥራው የማይሰለች እንዲሆን ማድረግ እንዲችሉ ማድረግ ይኖርበታል። እንዲሁም የሥራ ፍሰቱን ማፋጠን እና ቀጥታ ወደ ሶፍትዌርዎት ወይም ድር ጣቢያዎት በመተርጎም የሚያስፈልገውን የቴክኒክ ሥልጠና መቀነስ ይችላሉ።

ስለዚህ ዝርግ ሉህ በመጠቀም ሎካላይዝ ማድረግ ወይም ረጃጅም ኢሜይሎችን መላክ እና የገቡ መልእክቶች ውስጥ የሚፈልጉትን ለማግኘት ማሰስ አይጠበቅብዎትም። በተጨማሪም ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የሚያስችልዎትን የትርጉም ትውስታ እያከማቹ ይሄዳሉ። በሚሠራበት ቋንቋ ውስጥ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቃላትን በማስቀመጥ ተርጓሚዎችዎት ሥራው ላይ በፍጥነት እንዲጓዙ ያስችላቸዋል። ግዴታ እንደ ፕሮጀክት ማናጀር መሆን አለብኝ ወይም ቡድኑን መቆጣጠር አለብኝ ብለው የሚያስቡ ካልሆነ የትርጉም ሥራ አሠራር ሥርዓቱ የሥራ አመራር እና ቁጥጥር ሥራውን እንዲያከናውን ያድርጉት።

የሶፍትዌር ትርጉም መመሪያ

የሶፍትዌር ትርጉም በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ወደ ፊት ለመራመድ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ይመልከቱ እንዲሁም ውጤታማ የሆኑትን የአሠራር አካሄዶቻችንን ይከተሉ።

መመሪያውን ይመልከቱ

Leave a Reply